አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2015 ዓ.ም በአገራችን የመጀመሪያውና ብቸኛው የግል የቤት ብድር አቅራቢ ባንክ የሆነው ጎሕ ቤቶች ባንክ ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ጋር በጋራ መስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ፡፡ የመግባቢያ ሰነዱ በሁለቱ መስሪያ ቤቶች መካከል ያሉ የውክልና፣ የሽያጭና ሌሎች ተጓዳኝ የሰነድ አገልግሎቶችን ኮምፒዩተራይዝድ በሆነ የኦንላይን አማራጭ መንገድ መናበብ የሚያስችል ዘዴ ነው፡፡
እንደሚታወቀው ጎሕ ቤቶች ባንክ ሥራ ከጀመረበት ጥቅምት ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በነበረው የስምንት ወራት አገልግሎቱ ከ5800 በላይ ደንበኞችን ያፈራ ሲሆን፣ ለቤት መግዣ፣ መስሪያና ማደሻ የዋለ ገንዘብ ለተበዳሪዎች በመስጠት ያልተጣራ ትርፍ ብር 7.9ሚሊዮን (ሰባት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን) በማስመዝገብ የበጀት አመቱን አጠናቋል፡፡
ዛሬ የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድም ባንኩ ከ2012 ዓ.ም. ወዲህ በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት በኩል የተመዘገቡና ከባንኩ አገልግሎት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሰነዶችን በዳታቤዝ ሲስተሙ አማካኝነት በአካል በወረቀት ይዞ መሄድ ሳያስፈልግ በኦንላየን የሚከታተልና መፈጸም የሚችልበት ስርዓት ይሆናል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ህጋዊነት ያላቸው ሰነዶችን በተመለከተ በፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ያረጋገጣቸውንና የመዘገባቸውን ሰነዶች ጎሕ ቤቶች ባንክ በሁሉም ቅርንጫፎቹ መጠቀም የሚችልበት ቀላልና ወሳኝ አማራጭ በመሆኑ ለተገልጋዮቹ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል እንደሚሆን ታምኖበታል፡፡ በመሆኑም በዛሬው ቀን፤ በጎሕ ቤቶች ባንክ ዋና መ/ቤት የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ አስማረ እና የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ሐሚድ ኪኒሶ በተገኙበት የፊርማ ስነስርዓቱ ተካሂዷል፡፡